Login    Search   
  Tue, September 7, 2010
    This Week
     News
     Commentary
     ABBI Feature
  
   በዚህ ሳምንት
     ዜና
     የስኬት ፈርጦች
     ሳይንስና ቴክኖሎጂ
     ነጥብ
     እንዲህ ቢሆንስ
     አውደ ኪን
     ህግና ማኅበረሰብ

የአፍሪካ መሪዎች ራስ ምታት

ከጌታቸው ንጋቱ

·          መለስ ለኤርትራ ጉዳይ መቋጫ ይፈልጋሉ

·          ካቢላ የአባታቸው ዙፋን እያቃጠላቸው ነው

·          አዛውንቱና ታማሚው ዩሱፍ አልሆነላቸውም

·          የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ጉዳይ መሮታል

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሴኔጋል ዳካር  የኔፓድ ስብሰባ በቀጥታ ወደ ኒውዮርክ በማምራት ከፀጥታው ምክር ቤት ጋር በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በስብሰባው ላይ በአፍሪካ ያሉ የፀጥታ ችግሮች ላይ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከጥታው ምክር ቤት አባል አገራት መሪዎች ጋር የመከሩ ሲሆን የፀጥታው ምክር ቤት ጊዜውን በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ማጥፋት እንደመረረው ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ኀብረት የሰላምና ፀጥታ ሊቀመንበር  በመሆኗ እና በአፍሪካ ባላት ተሰሚነት በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተው በአፍሪካ ስላሉ የፀጥታ ችግሮች ዙሪያ ከፀጥታው ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላሉ ችግሮች ሁሉ መንስዔ ናት የምትላት ኤርትራ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠንከር ያለ እርምጃ ባለመውሰዱ ታማርራለች፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ ወስዶ ባለማወቁም የኤርትራ መንግስት የአንሚን ጦር እስከማባረር መድረሱንም ትጠቅሳለች፡፡

የኢትዮ- ኤርትራ ድንበር ያለ ሰላም አስከባሪ ባለበትና የሁለቱ አገራት ጦር ኃይሎች ተፋጠው በሚገኙበት ሁኔታ እንኳን፣ የፀጥታው ምክር ቤት አፋጣኝ እርምጃ አልወሰደም፡፡ በዚህም መለስ ደስተኛ አይደሉም፡፡ ለኦነግና ኦብነግ መጠለያ ሰጥቶ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት እንዲሰነዘሩ እያደረገ ከመሆኑም በለይ በሶማሊያ ባለው ችግር ላይ ነዳጅ እየደፋና እያቀጣጠለ እንደሚገኝ ኢትዮጵያ ትገልፃለች፡፡ የኤርትራ መንግስት በግልፅ የሶማሊያ ተቃዋሚዎች ደጋፊ መሆኑን ሲያምን ከምዕራባዊያን አገራት ጋርም ተቃርኗል፡፡

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት ለመግባት ምንም ዓይነት ፍላጐት እንደሌላት ብትገልፅም የፀጥታው ምክር ቤት እጁን አጣጥፎ መቀመጡ ጦርነቱን አይቀሬ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊም ጦርነት የማይቀር መሆኑን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስት መለስ የኤርትራ ጉዳይ የሶማሊያ ችግርና ሌሎችም አገራዊ ችግሮች ፈጣን ምላሽ እየጠየቋቸው የሚገኙ ሲሆን ከኒውዮርኩ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ በኤርትራ ጉዳይ አንድ ነገር ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤትም ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት የተሻለ አማራጭ ስለሌለው የመፍትሄ ኃሳቦቹን እየመረመረ ይገኛል፡፡ ኤርትራ ከየትኛውም የተባበሩት መንግስታት አካል ጋር ባለመተባበር የፀናች ስትሆን ኢትዮጵያም በኤርትራ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት በማለት የፀጥታው ምክር ቤትን እየወተወተች ትገኛለች፡፡

በአባታቸው መንበር ላይ ከተቀመጡ ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ሰላም ያላገኙት ካቢላም የሩዋንዳና ቡሩንዲ እንዲሁም የአገር ውስጥ አማፂያንና የስደተኞች ጉዳይ ሰላም ነስቷቸዋል፡፡ ለአገራቸው አንዴ ሰላም ወረደ ሲባል ሌላ ጊዜ ሲበጠበጥ ምንም ዓይነት የተረጋጋ አየር መተንፈስ ያልቻሉት ካቢላ፣ የአባታቸው መንበር  ምን ያህል እንደሚፋጅ የተረዱት ከመሆኑም በላይ እሳቸውም ባለው የፖለቲካ ትኩሣት ምክንያት እንደ አባታቸው ሕይወታቸው በተቃዋሚ እንዳይጠፋ ስጋት ስላላቸው በከፍተኛ የፀጥታ ክልል ውስጥ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት አቡድላሂ ዩሱፍ በአገራቸው ሶማሊያ ሰላም ሰፍኖ ሕግ ተከብሮ ማየት የናፈቃቸው ሲሆን፡፡ የሚቻል ግን አልሆነም፡፡

በኒውዮርኩ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይም የሰላም አስከባሪ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲልክ ጠይቀዋል፡፡ የትኛው አገር ሶማሊያ ጦሩን ለመላክ ይፈቅዳል የሚለው ግን አጠያያቂ ነው፡፡ አንድ ቀን በአገራቸው ሰላም ሰፍኖ እንደሚያዩ እርግጠኛ የሆኑት አብዱላሂ ዩሱፍ አሁን ነገሮች ግራ ሆነውባቸዋል፡፡ እድሚያቸው ገፍቷል፤ ከፍተኛ የጤና ቀውስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ አሁንም እየተሰደዱ ይገኛሉ፣ በየቀኑ ፍንዳታና የሞት ዜና በሶማሊያ አልቀረም፡፡ ይህም ከፍተኛ ራስ ምታት አስይዟቸዋል፡፡

ኬንያም በቋፍ ትገኛለች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች ከምርጫው በኋላ አልቀው መፍትሄ የተገኘ ቢመስልም አገሪቱ በማንኛውም ሰዓት ሊፈነዳ በሚችል የዘር ፓለቲካ ተወጥራ ትገኛለች፡፡ የዙምባብዌ የምርጫ ውጤት አለመገለፁን ተከትሎ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በማንኛውም ሰዓት ሊከሰት ይችላል የሚል ውጥረትም ሰፍኗል፡፡

ሮበርት ሙጋቤም በቀላሉ የሚለቁ አይመስሉም፡፡ ምዕራባዊያንም ሙጋቤን ለማጥቃት ይቋምጣሉ፡፡ ቻድ ከፈተኛ ቀውስና ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ የዳርፉር ጉዳይ መፍትሄ አጥቶ ሱዳናዊያን እየተገደሉና እየተሰደዱ ለመኖር ተገደዋል፡፡

ይህም ሆኖ ታዲያ የፀጥታው ምክር ቤት ለአንዱ ችግር እንኳን ምላሽ ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም አፍሪካ ውስጥ ሁሉምጋ እሳት መኖሩ፣ ሁሉም መሪዎች ራስ ምታት የያዛቸው መሆኑና፡፡

የፀጥታው ምክር ቤትም መታከቱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡

Designed and Developed by ReliIT