ሚያዚያ 5ቀን 2000 ዓ.ም በጠዋት ማልደው ወደ ቤተክርስቲያንና ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱ ሰዎች የተመለከቷት ፀሐይ ከወትሮው የተለየች ነበረች፡፡ ደርግ በ1983 ዓ.ም ሲወድቅ የታየችው አይነት ፀሀይ መሆኗን ብዙዎች ተናግረዋል፡፡ ፀሀይዋ የእግዚያብሔር ተዓምር መገለጫ ምልክት መሆኗንም የሀይማኖት አባቶች ገልፀዋል፡፡
ፀሀይዋ እስከ ቀትር ድረስ እየደበዘዘች ብትመጣም በቀለበት ታጥራ ረፋዱን ሞቅ ስታደርግ ውላለች፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ፀሀይዋን ቀና ብለው ባያዩም በዕለቱ የነበረውን የአየር ፀባይ እጅግ አድርገው እንደወደዱትና ዕለቱም የተባረከ ብሩህ ቀን ነው ሲሉ የተደመጡ አሉ፡፡
የፀሀይዋን አወጣጥ የተመለከቱት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቀጳጳስ አቡነ ጳውሎስ እና በኢትዮጰያ ለጉብኝት የተገኙት የአሌክሳንደሪያው ጳጳስ ቅዱስ ሺኖዳም ስለ ፀሀይዋ አስመልክተው የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ቢ.ቢ.ሲ ዘግቦታል፡፡
አቡነ ጳውሎስ ፀሀይዋ የበረከት ተምሳሌት መሆኗን ገልፀው "እግዚያብሔር ሆይ ስለ አሳየኸን የበረከት ምልክት እናመሰግንሃለን" ብለዋል፡፡
የአሌክሳደሪያው ጳጳስ ቅዱስ ሺኖዳም ፀሀይዋ የእግዚያብሔር በረከት መገለጫ መሆኗንና እግዚያብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን መባረኩን እንደሚያሣይ ገልፀዋል፡፡
በምርጫው ዕለት ፀሀይዋ መታየቷን ፖለቲካዊ እንድምታ አስይዘው የተናገሩ ሰዎች ሲኖሩ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ይህች ፀሀይ የዛሬ 17 ዓመት በኢትዮጵያ ታይታ ደርግ ከስልጣን መውረዱን ይሁን እንጂ በአሁኑ ምርጫ በኢትዮጵያ የአስተዳደርም ሆነ የመንግስት ለውጥ እንደማይጠበቅና የማይታሰብ መሆኑን አመልክቷል፡፡ |