Login    Search   
  Tue, September 7, 2010
    This Week
     News
     Commentary
     ABBI Feature
  
   በዚህ ሳምንት
     ዜና
     የስኬት ፈርጦች
     ሳይንስና ቴክኖሎጂ
     ነጥብ
     እንዲህ ቢሆንስ
     አውደ ኪን
     ህግና ማኅበረሰብ

የለገዳዲ ውሃ ማጣሪያ የመበከል አደጋ ተጋርጦበታል

ከዮሐንስ አንበርብር

ለአዲስ አበባ ከተማ በቀን 160ሺ ሜትሪክ ኪዩብ የመጠጥ ውሃ እያቀረበ የሚገኘው የለገዳዲ የውሃ ማጣሪያ ግድብ በአካባቢው በሚገኙ አርሶአደሮች የመበከል አደጋ ተጋርጦበታል፡፡

የውሃ ሀብት ሚኒስትሩ  አቶ አስፋው ዴንጋሞ  ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀማቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣ የምክር ቤቱ አባላት በአዲስ አበባ የውሃ ችግር ላይና በተለይም በለገዳዲ የውሃ ማጣሪያ ግድብ ላይ ከፍተኛ የብክለት አደጋ መጋረጡን በራሳቸው መንገድ ለመመልከት እንደቻሉና ባለሙያዎችንም አነጋግረው በአስቸኳይ የዕርምት ርምጃ ካልተወሰደ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ የጤና ጉዳት እንደሚደርስ የተገለፀላቸው መሆኑን ለሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ አስፋው ዴንጋሞ የተከሠተውን ችግር በወቅቱ ያረጋገጡ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተርም በመስሪያ ቤታቸው ላይ የክዋኔ ኦዲት በማድረግ ለተከሰተው ችግር በፍጥነት መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ እንዳሳሰቧቸው ጠቁመዋል፡፡

ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በግብርና የሚተዳደሩ ነዋሪዎች በአካባቢው ቢኖሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የነዋሪዎቹ ቁጥር በመብዛቱና ለመሬቶቻቸው የሚጠቀሙበት ማዳበሪያ እየታጠበ ወደ ውሃው በመቀላቀሉ ችግሩ ተከስቷል ብለዋል፡፡

የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ሚኒስትሩ፣ ግድቡን ተጠግተው የሚኖሩ አርሶአደሮችን ለማንሳት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሞክሩ አልያም ሌሎች የአካባቢ እንክብካቤ አማራጮችን እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ባለሙያ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው፣ በአካቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች መሬቱን ማረስ በመጀመራቸው አካባቢው መራቆቱን፣ በዚህም ምክንያት ዝናብ በሚጥልበት ወቅት አፈሩንና ማዳበሪያውን አጥቦ እንደሚገባ ይህ ደግሞ ለአልጌ መፈጠር ምቹ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ባለስልጣኑ ውሃውን ለማጣራት የሚያወጣውን ወጪ ከፍ እንዲል ያድርገበታል እንጂ ውሃው ሳይጣራ  አያልፍም ብለዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት እየቀረበ ያለው የመጠጥ ውሃ 240 ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 160 ሺ የሚሆነውን እያመረተ የሚገኘው የለገዳዲ ውሃ ማጣሪያ ግድብ ነው፡፡

የተቀረውን 80 ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ገፈርሳና ድሬ የተባሉት የውሃ ማጣሪያ ግድቦች ይሸፍኑታል፡፡

Designed and Developed by ReliIT