Login    Search   
  Tue, September 7, 2010
    This Week
     News
     Commentary
     ABBI Feature
  
   በዚህ ሳምንት
     ዜና
     የስኬት ፈርጦች
     ሳይንስና ቴክኖሎጂ
     ነጥብ
     እንዲህ ቢሆንስ
     አውደ ኪን
     ህግና ማኅበረሰብ

እነ ኢ/ርን ኃይሉ ምርጫ ቦርድ ላይ ክስ መሠረቱ

ከጌታቸው ንጋቱ

በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል የሚመራው የቀድሞው ቅንጅት ስሙ ለሌላ በመሰጠቱ በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ መሰረተ፡፡

ሚያዚያ 8/2000 ዓ.ም አዲስ አበባ ላለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት የደረሰው ክስ እንደሚገልፀው አራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መስከረም 14/1998 ውህደት መፈፀማቸውንና ውህደቱን የፈጸመው የቅንጅት ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰጠው የውህደቱን ሰነድ አያይዞ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጾ በአንቀጽ 24 መሠረት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት ሲገባው የምዝገባ ጥያቄው የተሟላ ባለመሆኑ ለቦርዱ አይቀርብም ሲል በጽሕፈት ቤት በኩል መልስ መስጠቱ ተገቢ እንዳልነበር ይገልጻል፡፡

ቅንጅት ምርጫ ቦርድ እውቅና ሰጥቶ የ1997 ብሔራዊ ምርጫ የተወዳደረ ሲሆን የቅንጅት አመራር ተከሶ እስከ እድሜ ልክ እስራት ድረስ ተፈርዶበት አመራሮቹ በይቅርታ ሲለቀቁ ከገዢው ፓርቲ ጋር ውይይቱ እንደሚቀጥል በአገር ሽማግሌዎች አማካይነት ከመንግሥት ቃል ተገብቶ እንደነበር የክሱ ቻርጅ ይዘረዝራል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 46/86 አንቀጽ 25 (2) መሠረት ጥያቄውን ለቦርዱ ካቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ሕጋዊ ሰውነት እንዳለው ሆኖ የሚቆጠር መሆኑ እየታወቀ የቅንጅት ስም ለአንድ ሌላ አካል፣ እንዲሁም የቅንጅትን ፓርቲ አርማ ለሌላ አካል በመስጠት ከሕግ አግባብ ውጭ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ቦርዱ መፈፀሙን በክስ ማመልከቻው ላይ ተገልጿል፡፡ በምርጫ ቦርድ ላይ የቀረበውን የክስ አቤቱታ የፍርድ ቤቱ ሪጅስትራር የተቀበለ ሲሆን ሪጅስትራሩ ፋይሉን ለዳኞች አቅርቦ ተጠሪው የሚቀርብበትን ጊዜ የሚወስንበት ሂደት እየተጠበቀ መሆኑን ከቀድሞው የቅንጅት ጽ/ቤት የተገኘው ዜና ያመለክታል::

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ሕጋዊ ስያሜ ለአቶ አየለ ጫሚሶ የተሰጠ ሲሆን ቅንጅቱ የአራት ፓርቲ በነበረበት ወቅት በምርጫ 97 የተጠቀመበት የጣት ምልክት የቅንጅቱ አባል ለነበረውና በአቶ ልደቱ አያሌው ለሚመራው ኢዴአፓ- መድህን መሰጠቱ ይታወቃል፡፡

Designed and Developed by ReliIT