Login    Search   
  Tue, September 7, 2010
    This Week
     News
     Commentary
     ABBI Feature
  
   በዚህ ሳምንት
     ዜና
     የስኬት ፈርጦች
     ሳይንስና ቴክኖሎጂ
     ነጥብ
     እንዲህ ቢሆንስ
     አውደ ኪን
     ህግና ማኅበረሰብ
መከላከያ ሚኒስቴርና የእንግሊዝ ኤምባሲ የስልጠና ስምምነት ተፈራረሙ
ከጌታቸው ንጋቱ

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስቴርና የእንግሊዝ ኤምባሲ በትናንትናው እለት የስልጠና ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ወታደሮች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት በመስጠት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ የሰላም ማስከበር ሥራዎች ውጤታማ ለማድረግ የታቀደ ነው፡፡

የእንግሊዝ ኤምባሲ አምባሳደር ሚስተር ኖርማን ሊንግ እና የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሣሁን ደንድር በትናንትናው ዕለት የስምምነቱን የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን ኢትዮጵያ በውጭ አገራት በሚደረጉ የሰላም ማስከበር ሥራዎች ላይ በስፋት እንድትሳተፍ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ስምምነቱን ተከትሎ የእንግሊዝ ኤምባሲ አምባሳደር ሊንግ እንደተናገሩት "የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስቴርን በመርዳታችን ደስተኞች ነን፡፡ ይህም የሚኒስቴሩን የሰው ኃይል የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ያሳድጋል፡፡

"ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የሰላም አስከባሪ በማቅረብ ግንባር ቀደም አገር ናት፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ውስጥ በመሳተፍ 7ኛ ደረጃ  ላይ ትገኛለች፡፡ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲና በዳርፉር የኢትዮጵያ ሠራዊት ታላቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ስልጠናም የኢትዮጵያ ኃይል ውጤታማ በሆነ መልኩ በአፍሪካ ኀብረትና በተባበሩት መንግስታት ልዑካን እንዲሳተፍ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን በበኩላቸው "የእንግሊዘኛ ቋንቋ ስልጠናው ጊዜውን የጠበቀ፣ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለውና ለፍላጐታችን ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም የመከላከያ ሚኒስቴሩ የተሟላና ራሱን የቻለ ብቁ የእንግሊዘኛ ቋንቋ የስልጠና ስርዓት እንዲኖረው ያደርጋል፤ ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታደርገውን የሰላም ማስከበር ሥራ አጠናክራ እንድትቀጥል ያደርጋል" ብለዋል፡፡

ይህ  የእንግሊዝ መንግስት ለተለያዩ አገራት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ስልጠናን የመስጠት ፕሮጄክት ውጤታማ የሰላም ማስከበርና የሰብዓዊ አገልግሎት እንዲሠራ የሚያደርግ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ በቂ ኃይል ኖሮአት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ የሰላም ማስከበር ሥራ እንድታከናውን እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡

ወደተለያዩ አገራት የሚላኩ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች የግድ የአፍሪካ ኀብረት የቋንቋ መስፈረትን ማሟላት የሚገባቸው ሲሆን ስልጠናው በኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ አበባና በክልል በሚገኙ የመከላከያ ማሰልጠኛዎች እንደሚሠጥ ተገልጿል፡፡ ለስልጠናው የመጀመሪያ ዓመት ወጪ 3.8 ሚሊዮን ብር የእንግሊዝ መንግስት መመደቡን እና መከላከያ ሚኒስቴር ለስልጠናው ተጨማሪ ወጪ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Designed and Developed by ReliIT