|
በአካባቢና የማሟያ ምርጫ ከመወዳደር ራሳቸውን ያገለሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ኀብረት (ኢዴኃ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ሕጋዊ ሰውነት ሊነሳ እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ የሁለቱንም ፓርቲዎች ድርጊት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አወገዘ፡፡
በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው ኀብረት ወደ ምርጫው ከመግባቱ በፊት ቀደም ብሎ የወጣ ሲሆን በአቶ ቡልቻ የሚመራው ኦፍዴን ግን በሚያዚያ 5ቱ ምርጫ ከተወዳደረ በኋላ ከትናንት በስቲያ በሰጠው ይፋዊ መግለጫ ራሱን ከምርጫው ማግለሉን አስታወቋል፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ለመወዳደር ፍትሃዊ የሆነ የመወዳደሪያ መድረክ የለም በማለት የተናገሩ ሲሆን ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ፓርቲዎቹ የወሰዱት እርምጃ ተገቢ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡
የሁለቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውሣኔ አስመልክቶ ፓርቲው በተናጠል መግለጫ የሰጠ ሲሆን በፓርቲዎቹ ላይ በሚወሰደው እርምጃ ዙሪያ ውሣኔ እንዳልተላለፈ የቦርዱ ኃላፊ ዶ/ር መርጋ በቃና ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በፖለቲካ ፓርቲዎች የመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 38 መሠረት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ወቅት ምርጫውን አቋርጦ ቢወጣ ሕጋዊ ሰውነት ሊያሳጣ የሚያስችል እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችልም ተገልጿል፡፡ የቦርዱ ሊቀመንበር ዶ/ር መርጋ እንደተናገሩት ጉዳዩን ቦርዱ እንደሚመክርበትና አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ መወሰድ ካለበትም እንደሚተላለፍ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫም ፓለቲካ ፓርቲዎቹ ብዙ ሃብትና ንብረት ለምርጫው ዝግጅት ከወጣ በኋላ ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውና ጥለው መውጣታቸው ተገቢ አለመሆኑን፤ ቦርዱ፣ ተቃዋሚዎቹ አለብን ያሉትን ችግር ለመረዳት አቅርቡ ብሏቸው ማስረጃ ማቅረብ አለመቻላቸውን አመልክቷል፡፡ በቦርዱ ላይም የስም ማጥፋት ሥራ ከመስራት የተሻለ ችግሮች ካሉ ሊፈቱ የሚያስችሉ ምንም ዓይነት መረጃ ይዘው እንዳልቀረቡም በተሰጠው መግለጫ ተመልክቷል፡፡
ተቃዋሚዎቹ እጅግ አነስተኛ ዕጩዎች ብቻ ለምርጫው በማቅረባቸውና በምርጫው ለማሸነፍ ተስፋ የለንም ብለው ስለሚያስቡ፣ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ ብቻ በሚል ከምርጫው ወጥተዋል የሚለውን ሃሣብ እንደሚጋሩትም የጽ/ቤቱ ዋና ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡
ባለፈው እሁድ ምርጫ 9ዐ በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ መምረጡን ቦርዱ ሲያስታውቅ፣ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረው የታዘቡ ጋዜጠኞች ብዙ መራጭ አለማየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ የቦርዱ ኃላፊዎች እንዳስረዱት በመላ አገሪቱ 42 ሺ እንዲሁም በአዲስ አበባ 1 ሺ 770 የምርጫ ጣቢያዎች ስላሉ ሰው በአቅራቢያው ባሉ ጣቢያዎች መምረጡን በማስረጃ የተደገፈ መረጃ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ያለፈውን ምርጫ ስኬታማ፣ ሰላማዊና የሕዝብ ንቁ ተሣትፎ የተስተዋለበት በማለት ሲገልፅ፣ ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉት ፓርቲዎች ቢሸነፉ እንኳን አሸናፊውን እንኳን ደስ አለህ ብለው ለሚቀጥለው ምርጫ ጠንክረው መስራት ይገባቸው እንደነበርና ተቃዋሚዎች ይህንን ማድረጋቸው ለዴሞክራሲያዊው ስርዓት ግንባታ ምንም ደንታ የሌላቸው መሆኑን እንደሚይሳይም የቦርዱ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ከምርጫ 97ትም ምንም ትምህርትና ተሞክሮ ሁለቱ ፓርቲዎች አለመውሰዳቸውን የቦርዱ ፀሐፊዎች ገልፀዋል፡፡ |