Login    Search   
   Date: 2008-04-18   Volume: 3    Issue: 36
  Tue, September 7, 2010
    This Week
     News
     Commentary
     ABBI Feature
  
   በዚህ ሳምንት
     ዜና
     የስኬት ፈርጦች
     ሳይንስና ቴክኖሎጂ
     ነጥብ
     እንዲህ ቢሆንስ
     አውደ ኪን
     ህግና ማኅበረሰብ

ከአወዛጋቢው ዓባይ ገባሮች በአንዱ ግንባታ ተጀመረ

ከዮሐንስ አንበርብር

ግብጽና ሱዳን በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ አስር ዓመታትን የፈጀ ውይይት ከተፋሰስ ሀገራት ጋር ቢያደርጉም ኢትዮጵያ የተፋሰሱን አጠቃቀም አስመልክቶ ባስቀመጠችው ነጥብ ላይ ለመግባባት አልቻሉም፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ካቀደቻቸው አምስት የአባይ ገባር ወንዝ ግድብ እቅዶች የአንዱን ግንባታ ጀምራለች፡፡

የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ሚኒስትር የሆኑት አቶ አስፋው ዴንጋሞ ባለፈው ማክሰኞ እለት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረቡት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ስምምነት ሊደረስበት ያልቻለበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጋት የህግ ክልከላ ሳይሆን ድህነትና የዕውቀት ማነስ መሆኑን የሚናገሩት ሚኒስትሩ፣ በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን (ተፋሰሶችን) አስመልክቶ የተቀመጡ ህጎች ሁለት መሆናቸውን ////፡፡

ፍትሃዊና ርተአዊ የውሃ አጠቃቀም (equitable and reasonable water utilization)  እና በውሃው ላይ ተጨባጭ የሆነ ጉዳት አለማድረስ (utilizing without causing significant harm/ የሚሉት መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያን የሚጐዳ አለም አቀፍ ህግ ባለመኖሩ ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ድርድር እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ያለፉትን 10 ዓመታት የፈጀው ድርድር 89 አንቀጾችና 66 ንዑስ አንቀጾች ሲኖሩት ከዚህ ውስጥ ስምምነት ያልተደረሰው በአንድ አንቀፅ ላይ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ግብፅና ሱዳን ያልተሰማሙበት አንቀፅ በኢትዮጵያ የቀረበ ሲሆን የውሃውን ደህንነት በተጨባጭ በማይጐዳ መልክ መጠቀም (not to significantly affect the water security of any of the Nile basin) የሚል ሲሆን ሌሎቹ ሰባት ሀገራት ተስማምተውበታል፡፡

ግብፅና ሱዳን ግን አንቀጽ ላይ፣ አሁን ያለው የውሃው መጠን እንዳይቀንስና እየተጠቀሙበት ያሉት አገሮች የሚደርሳቸው መጠን እንዳይቀንስ (not to adversely affect the water security and current uses & rights) የሚል እንዲጨመርላቸው ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ኃሳብ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ የተቀሩት አገራት መስማማት እንዳልቻሉ አቶ አስፋው ዴንጋሞ ገልፀዋል፡፡

በዚህ ነጥብ ላይ መስማማት ባለመቻሉ ሙሉ ስምምነቱ ላይ ነጥብ የጣለ ቢሆንም ሀገሮቻችውን ወክለው የሚደረደሩት ሚኒስትሮች አለመግባባቱን ለማስወገድ ሌሎች የልማት ስራዎች በጋራ እየተከናወኑ፣ መግባባት ባልተደረሰበት አንቀፅ ላይ ሁሉም ሀገራት የሚወከሉበት የአባይ ኮሚሽን ተቋቁም ለመነጋገር ሙከራ ይደረግ የሚል ኃሳብ ማቅረባቸውን የሚንስትሩ ገለፃ ያስረዳል፡፡

ነገር ግን የተፋሰሱ ሀገራት መረጃዎች ፖለቲካዊ እይታ ሊኖራቸው ስለሚችል ለመሪዎቹ ይመራ የሚል ኃሳብ ቀርቦ በማሸነፉ ይኸው ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

ግብፅ የምትከራከረው በዚህ ብቻ ሳይሆን፣ የአባይ ወንዝ መጠን 166ዐ ቢሊዮን ሚትሪክ ኪዩብ መሆኑንና ወደ ግብፅ የሚሂደው ደግሞ የዚህ ከ4 እስከ 3 በመቶው ብቻ መሆኑን ፣ ስለሆነም ኢትዮጵያ ይህንን ያህል እየተጠቀመች በጠብታ ከሚደርሰን ላይ መጠኑን መቀነስ የለባትም የሚል ጫና ለማሳደርም እንደምትሞክር ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

በዓለም ህግ መሠረት ግን ድንበር የተሻገረ ተፋሰስ ማለት ተፋሰሱን ብቻ (Green water) እንጂ በዝናብ የሚጨመርለትንና ከከርስ ምድር የሚያገኘውን የማያጠቃልል ሲሆን፣ በግብፅ በኩል እየተጠቀሰ ያለው ቁጥር ግን የተጠቀሱትን የጨመረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ባላት አቅም አምስት ግድቦችን በአባይ ዙሪያ ልትገነባ መሆኗን የሚናገሩት ሚኒስትሩ በቀጥታ ወደ አባይ የሚቀላቀለውን ረብ በተባለው ወንዝና መገጭ፣ ሀመርና ጀዋ ላይ ግንባታ ለማካሄድ ጥናት ልታደርግ ሲሆን ግንባታው የተጀመረ መኖሩንም ገልፀዋል፡፡

ግብፅ እምቢተኛነቷን ትታ ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መገኘትም ድል ነው ብለዋል የውሃ ሀብት ሚንስትሩ አቶ አስፋው ዲንጋሞ፡፡

Designed and Developed by ReliIT