Login    Search   
  Tue, September 7, 2010
    This Week
     News
     Commentary
     ABBI Feature
  
   በዚህ ሳምንት
     ዜና
     የስኬት ፈርጦች
     ሳይንስና ቴክኖሎጂ
     ነጥብ
     እንዲህ ቢሆንስ
     አውደ ኪን
     ህግና ማኅበረሰብ

ቴዲ አፍሮን ዘብጥያ ያወረደ የሞት አደጋ

ከዮሐንስ አንበርብር

ዝነኛው አርቲስት ቴድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ጥር 23 ቀን 1999 ዓ.ም ነበር ከካናዳ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው፡፡ የዚያን ቀን ሌሊት ግን ምናልባትም ለሁለት ሰዎች ክፉ እጣ ነበር፡፡ ለቴዲ አፍሮና ለደጉ ይበልጣል፡፡ ከካናዳ ለመጣው ዝነኛ አርቲስትና በጎዳና ላይ ለሚኖረው ቤተሰብ አልባው ዜጋ፡፡ (ወረዳ 17)  

ጥር 23 ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ ነው በተለምዶ ፊት በር ወይም ሸራተን አካባቢ የአንድ ግለሰብ አስክሬን በፖሊስ ይገኛል፡፡ ይህ ግለሰብ በመኪና ተገጭቶ መሞቱን ለማረጋገጥ ከባድ አልነበረም፡፡ ፈታኙ ነገር ግን ይህንን ግለሰብ ማን ገደለው ወይም ማን ገጨው? የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡

ፖሊስ በደጉ ይበልጣል አስከሬን ላይ ምርመራውን እያካሄደ በአካባቢው ከነበሩ የዓይን እማኞች መረጃዎችን መሰብሰብ ጀመረ፡፡

በወቅቱ በዓይን እማኝነት መረጃ በማቀበል ፖሊስን እንደ ተባበሩ ከተገለፀላቸው መካከል በሌሊት የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ወጣት ነበር፡፡ ይህ የታክሲ ሹፌር አደጋ አድርሶ ያመለጠውን ተሽከርካሪ በመከታተል ታርጋውን ለፖሊስ ለማቀበል እንደቻለ በወቅቱ የቀረበው የፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡

ፖሊስ በታክሲ ሹፌሩ አማካኝነት የቀረበለትን መረጃ በመንተራስ አደጋ አድርሶ የተሰወረ በሚል የጠረጠረውን ተሽከርካሪ በመፈለግ ሊያገኘው ችሏል፡፡ በታክሲ ሹፌሩ የተሰጠው የሠሌዳ ቁጥር የቴዲ አፍሮ ቢኤም ደብሊው ተሽከርካሪ ነበረች፡፡

ፖሊስ ይህንንና ሌሎች መረጃዎችን በማጠናከር ተጠርጣሪውን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የተሟላ መረጃ ስላልነበረው ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፖሊስ በ7 ቀን ውስጥ ምርመራውን አጠናቆ ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ያዛል፡፡

ፖሊስ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ባለመቻሉ አርቲስት ቴዲ አፍሮን ፖሊስ ራሱ በነፃ ያስናብተዋል፡፡ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በወቅቱ ክስ ያልተመሰረተና ጉዳዩም ከፖሊስ ወደ አቃቤ ህግ ያልተላለፈ መሆኑን ነው፡፡

ቴዲ አፍሮ በፖሊስ ለቀረበለት ጥርጣሬ የሰጠው ምላሽ ከፖሊስ መረጃ ጋር የማይስማማ ነበር፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው የቴዲ አፍሮ ቢ ኤም ደብሊው በወቀቱ ግጭት ደርሶባት ነበር፡፡ እንዴት? ቴዲ አፍሮ ለዚህ ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡

ጥር 23 ቀን ከካናዳ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰበት ቀን ነበር፡፡ ሌሊቱን ሲዝናና አምሽቶ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡ በጉዞ ተዳክሞ እንደ ነበር የሚናገረው ይኸው አርቲስት እዛው ቤቱ መዳረሻ አካባቢ ከድካም የተነሳ ከግንብ ጋር ይጋጫል፡፡ እናም በሰው ላይ ሳይሆን አደጋ ያደረሰው በራሱ ላይ መሆኑን ይናገራል፡፡

በቂ መረጃ ያላገኘው ፖሊስ ላለፉት አንድ ዓመት ከሦስት ወራት መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቶ ባለፈው ረቡዕ እለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት አዲስ ክስ ይመሰርታል፡፡ ይኸው ክስ በተመሳሳይ ሁኔታ ቴዲ አፍሮን በደጉ ይበልጣል ሞት የሚጠረጥር ነው፡፡  

አዲሱ ክስ ቴዲ አፍሮን ሰው በመግጨት፣ የተገጨውን ሰው መርዳት እየቻለ ባለማድረጉ እንዲሁም በወቅቱ መንጃ ፈቃድ ይዞ ባለማሽከርከር የሚወነጅል ነው፡፡  ዋነኛው ክስ መርዳት እየቻለ ባለማድረጉ የሚለው ሲሆን፣ በአዲሱ አዋጅ 543/3 መሠረት ከ5-15 ዓመት የሚያስቀጣ ነው፡፡

ባለፈው ረቡዕ በዋለው ችሎት ላይ ጠበቃው አቶ ሚሊዮን፣ ደንበኛቸው ቴዲ አፍሮ ይህ አንቀጽ ሊጠቀስበት አይገባም የሚል ክርክር አንስተዋል፡፡ አቃቢ ህግ ይህንን አንቀጽ ለመጥቀስ ያበቁትን መረጃዎች አቅርቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠበቃው ዋስትና የጠየቀ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ያሰጣል ወይስ አያሰጥም የሚለውን ጉዳይ ለማየትና የተከሳሹን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማትና ውሳኔ ለመስጠት ለመጪው ሰኞ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፣ እስከ ቀጠሮው ቀን ድረስ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

አርቲስት ቴዲ ላይ ፍርድ ቤቱ ከላይ የተጠቀሰውን ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ወደ ማረፊያ ቤት እስኪወሰድ ድረስ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኝ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ አጠገብ ከሚገኝ የጥበቃ ቤት ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

በፍ/ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ ባለጉዳዮች፣ የቴዲን ጉዳይ ሲከታተሉ የነበሩ ዘመዶች፣ ጓደኞችና አርቲስቶች፣ ቴዲን በመክበብ ለፖሊስ ችግር በመፍጠራቸው ቴዲ ከእስረኞች ጋር እንዲቀላቀል ተደርጎ፣ ዘጠኝ ሰዓት ከ20 አካባቢ ወደ ማረፊያ ቤት ተወስዷል፡፡

Designed and Developed by ReliIT